Psalms 79

ብሔራዊ ሰቈቃ

የአሳፍ መዝሙር።

1አምላክ ሆይ፤ ሕዝቦች ርስትህን ወረሩ፤
የተቀደሰውን ቤተ መቅደስህን አረከሱ፤
ኢየሩሳሌምንም አፈራርሰው ጣሏት።
2የባሪያዎችህን ሬሳ ለሰማይ ወፎች፣
የቅዱሳንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት፣
ምግብ አድርገው ሰጡ።
3ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ፣
እንደ ውሃ አፈሰሱ፤
የሚቀብራቸውም አልተገኘም።
4እኛም ለጎረቤቶቻችን መዘባበቻ፣
በዙሪያችንም ላሉት መሣቂያ መሣለቂያ ሆንን።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ነው?
የምትቈጣውስ ለዘላለም ነውን?
ቅናትህስ እንደ እሳት ሲነድድ ይኖራልን?
6በማያውቁህ ሕዝቦች ላይ፣
ስምህን በማይጠሩ፣
መንግሥታት ላይ፣
መዓትህን አፍስስ፤
7ያዕቆብን በልተውታልና፤
መኖሪያ ቦታውንም ባድማ አድርገዋል።

8የአባቶቻችንን ኀጢአት በእኛ ላይ አትቍጠርብን፤
ምሕረትህ ፈጥና ወደ እኛ ትምጣ፤
በጭንቅ ላይ እንገኛለንና።
9አዳኛችን የሆንህ አምላክ ሆይ፤
ስለ ስምህ ክብር ብለህ ርዳን፤
ስለ ስምህ ስትል፣
ታደገን፤ ኀጢአታችንንም ይቅር በል።
10ሕዝቦች፣ “አምላካቸው የት አለ?”
ለምን ይበሉ?

የፈሰሰውን የአገልጋዮችህን ደም በቀል፣
ዐይናችን እያየ ሕዝቦች ይወቁት።
11የእስረኞች ሰቈቃ በፊትህ ይድረስ፤
በክንድህም ብርታት፣
ሞት የተፈረደባቸውን አድን።

12ጌታ ሆይ፤ ጎረቤቶቻችን በአንተ ላይ የተዘባበቱትን መዘባበት፣
ሰባት ዕጥፍ አድርገህ አስታቅፋቸው።
13እኛ ሕዝብህ፣ የማሰማሪያህ በጎችህ፣
ለዘላለም ምስጋና እናቀርብልሃለን፤
ከትውልድ እስከ ትውልድም፣
ውለታህን እንናገራለን።
Copyright information for AmhNASV